Ahadu Radio And Television
Ahadu Radio And Television
June 17, 2025 at 09:55 AM
*እስራኤል በሰጠችው ትዕዛዝ መሠረት ኢራናዊን ሀገራቸውን ለቀው እየወጡ መሆኑ ተገለጸ* ሰኔ 10/2017 (አሐዱ ሬዲዮ) በርካታ የዓለም ሀገራት ዜጎቻቸው ከኢራን ለቀው እንዲወጡ ትዕዛዝ እየሰጡ ባለበት በዚህ ወቅት፤ ኢራናዊያንም  ከቴህራን ለቀው እየወጡ መሆኑን የሚያሳዩ የቪድዮ ምስሎች ከሀገሪቱ እየወጡ ይገኛሉ። ለአብነትም በቴህራን የሚገኙ አውራ ጎዳናዎች ወደ ምዕራብ አቅጣጫ እያቀኑ ባሉ መኪኖች መጨናነቅ መኖሩን የሚያሳዩ ቪድዮች በማህበራዊ ሚዲያዎች ላይ በስፋት በመሠራጨት ላይ ናቸው። የአሜሪካ ፕሬዚዳንት ዶናልድ ትራምፕ ቀደም ሲል በማህበራዊ ሚዲያ ገጻቸው "ነዋሪዎች በሙሉ ከቴህራን በአስቸኳይ ለቀው እንዲወጡ" ያስጠነቀቁ ሲሆን፤ "ቴህራን ሙሉ በሙሉ እንድትወድም" ሲሉም ትዕዛዝ ሰጥተዋል። የእስራኤል ጦር ከዚያ ቀደም ብሎ ነዋሪዎች ከሰሜን ምስራቅ ቴህራን ለቀው እንዲወጡ ማስጠንቀቂያ አውጥቶ እንደነበር ይታወሳል። የእስራኤል ጠቅላይ ሚኒስትር ቤኒያሚን ኔታንያ "የኢራንን የአየር ክልል በእጃችን አስገብተናል" ሲሉ የገለጹ ሲሆን፤ የኢራን የጦር ጄነራሎች ወደ ሩሲያ እየሸሹ መሆናቸውን ዓለም አቀፍ የብዙሃን የመገናኛ አውታሮች እየዘገቡ  ይገኛሉ። እንዲሁም የኢራን የመንግሥት የቴለቭዥን ጣቢያ በትናንትናው ዕለት በእስራኤል ጥቃት ደርሶበታል ነው የተባለዉ። በዚህ ድንበር ተሻጋሪ ጦርነት እስራኤል በቴህራን ላይ እያነጣጠረች ያለው፤ በመከላከያ ሚኒስቴር መስሪያ ቤት፣ በውጭ ጉዳይ መስሪያ ቤት እና በኒዉክሌር መሰረተ ልማት ግንባታዎች ላይ መሆኑ ታውቋል። በዚህም የእስራኤሉ የስለላ ድርጅት 'ሞሳድ' በቴህራን ውስጥ በርካታ ሰላዮችን ቀድሞ ማስገባቱ የተነገረ ሲሆን፤ 'ኢራን ጥቃቱን ለመከላከል አስቸጋሪ አድርጎባታል' ተብሏል። በምካከለኛው ምስራቅ ለረጅም ዓመታት ፖለቲካዊ ውዝግብ ውስጥ ገብተው የቆዩት ቴህራንና ቴል አቪቭ ምንም እንኳን የሚያዋስናቸዉ አንዳችም ድንበር ባይኖራቸውም፤ ጦርነቱን ድንበር ተሻጋሪ የአየር ጥቃት አድርገውት ቀጥለዋል። በጦርነት ሂደት ውስጥ የሕዝብ ብዛት ሚና እንደሚጫወት የሚታወቅ ሲሆን፤ የእስራኤል የሕዝብ ብዛት ከ10 ሚሊዮን በታች እንደሆነ ሲገለፅ፤ ነገር ግን ኢራን ከ80 ሚሊዮን በላይ ሕዝብ ያላት ሀገር ናት ተብሏል። ይህ የሁለት ሃያላን መንግሥታት ድንበር ተሻጋሪ ጦርነት ገና ከጅምሩ ስጋት የደቀነ ሲሆን፤ በጦርነቱ በርካታ ሀገራት ተዋናይ እየሆኑ ነው። በደረጄ መንግስቱ #አሐዱ_የኢትዮጵያውያን_ድምጽ *ትክክለኛዎቹን የአሐዱ ራዲዮ የማህበራዊ ሚዲያ ገጾች በመቀላቀል ቤተሰብ ይሁኑ!* ፌስቡክ: https://www.facebook.com/ahaduradio ድረ ገጽ፡- https://ahaduradio.com/ ዩትዩብ፦ http://shorturl.at/cknFP ቲክቶክ ፡- www.tiktok.com/@ahadutv.official ዋትስአፕ፦ whatsapp.com/channel/0029VajDfVZI1rcb05C5B22b አስተያየት እና ጥቆማ ለመስጠት በ7545 አጭር የፅሁፍ መልክት ይላኩ
Image from Ahadu Radio And Television: *እስራኤል በሰጠችው ትዕዛዝ መሠረት ኢራናዊን ሀገራቸውን ለቀው እየወጡ መሆኑ ተገለጸ*   ሰኔ 10/2017 (አ...

Comments