Ahadu Radio And Television
Ahadu Radio And Television
June 17, 2025 at 04:45 PM
*በዋግኽምራ ዞን ዝቋላ ወረዳ 35 ሺሕ ዜጎች ለረሀብ መጋለጣቸው ተገለጸ* ሰኔ 10/2017 (አሐዱ ሬዲዮ) በአማራ ክልል ዋግኽምራ ዞን ዝቋላ ወረዳ 35 ሺሕ ዜጎች ለረሃብ መጋለጣቸውን እና አስቸኳይ ድጋፍ ማድረስ ካልተቻለ ከፍተኛ የሆነ የሞት አደጋ ሊከሰት እንደሚችል የወረዳው ዋና አስተዳዳሪ ታፈረ ምሳ ለአሐዱ አስታውቋል። 'ለምን ያህል ዜጎች እርዳታ ያስፈልጋል?' የሚለው በወረዳው የምግብ ዋስትና እና በዞን ምግብ ዋስትና የተጠና ቢሆንም፤ ከመስከረም ወር ወዲህ ዜጎች ድጋፍ አለማግኘታቸውን ተናግረዋል። የርሃብ አደጋው የተከሰተው ባለፈው ዓመት ክረምት ወቅት ከፍተኛ ዝናብ በመዝነቡ በጎርፍ አደጋ ከፍተኛ መጠን ያለው ሰብል በመውደሙ እንደሆነም ዋና አስተዳዳሪው ገልፈዋል። የዝቋላ ወረዳ ቅድመ ማስጠንቀቂያ የሥራ ሂደት ቡድን አስተባባሪ አቶ ወርቁ ሳህሌ በበኩላቸው በወረዳው እና በዞን የተጠና ጥናት እንደነበር ጠቁመው፤ "ድጋፍ ለሚያስፈልጋቸው ዜጎች ከመስከረም ወር ጀምሮ ምንም አይነት ድጋፍ አልደረሳቸውም" ሲሉ ገልጸዋል። "እየተከሰተ ያለውን ችግር ለመቀነስ ከግብረ ሰናይ ድርጅቶች ጋር ንግግር እያደረግን ነው" ሲሉ የገለጹት አስተባባሪው፤ በዚህም "ኒውትራል ፌደሬሽን" የሚባል ድርጅት ለ196 ሰዎች የገንዘብ ድጋፍ ለማድረግ የሂሳብ ቁጥር የመሰብሰብ ሥራ እየሰራ እንደሚገኝ አስታውቀዋል። የክልሉ መንግሥት ከፍተኛ ችግር ውስጥ ላሉ ዜጎች 27 ሺሕ 100 ኩንታል የምግብ ድጋፍ መድቦ ከዚህም ውስጥ 2 ሺህ 38 ኩንታል ብቻ ወረዳው ላይ መድረስ መቻሉን ገልጸው፤ የመጣው ድጋፍ ካለው ችግር አንፃር በቂ አለመሆኑን ተናግረዋል። አስተባባሪው አክለውም ከክልል የተደረገውን ድጋፍ በነዳጅ ችግር ምክንያት ለዜጎች ማድረስ እንዳልተቻለ አስታውቀዋል። "ዜጎቹን ከተጋረጠባቸው አደጋ በዘላቂነት ለመታደግ በተደጋጋሚ ለዞን ሪፖርት ብናደርግም፤ አጥጋቢ ምላሽ ማግኘት አልቻልንም" ብለዋል። በዚህም አሐዱ "በዞኑ የተከሰተውን ችግር ለመፍታት ምን እየተሰራ ነው?" ሲል የአማራ ክልል አደጋ መከላከል እና ምግብ ዋስትና ኮሚሽን የቅድመ ማስጠንቀቂያ ምላሽ ዳይሬክተር የሆኑትን አቶ ብርሃኑ ዘውዱን ጠይቋል። በምላሹም በክልሉ በተፈጥሮ እና ሰው ሰራሽ ችግሮች ምክንያት ድጋፍ የሚደረግላቸው አካባቢዎች መኖራቸውን እና ከእነዚህ አካባቢዎች አንዱ ዋኽምራ ዞን የሚገኘው ዝቋላ ወረዳ አንዱ መሆኑን ገልጸዋል፡፡ ዳይሬክተሩ አክለውም፤ "ክልሉ እርዳታ ለሚያስፈልጋቸው ዜጎች ባለፈው ሳምንት ድጋፍ አድርጓል" ብለዋል። ከዞን አመራሮች ጋር በመነጋገርም ድጋፍ በከተማ ከሚገኙት ውጭ ለገጠሩ ህብረተሰብ ለማዳረስ እየተሰራ ስለመሆኑም አስታውቀዋል። "ሆኖም ከዚህ በኋላ ሁሉም ችግር በበላይ አካላት ይፈታል ተብሎ መታሰብ የለበትም እስካሁን ባለው አስፈላጊው ድጋፍ ተደርጎላቸዋል" ሲሉ ለአሐዱ ተናግረዋል። ዳይሬክተሩ 'ክልሉ ባለፈው ሳምንት ድጋፍ አድርጓል' ሲሉ ቢገልጹም፤ የወረዳው ቅድመ ማስጠንቀቂያ ቡድን አስተባባሪ ግን "ዜጎቹ ከመስከረም ጀምሮ ድጋፍ ሳይደግላቸው ቆይተው ተደርጓል የተባለው ድጋፍም በነዳጅ እጥረት ምክንያት አልደረሰም" ብለዋል፡፡ በህይወቴ ጌትነት #አሐዱ_የኢትዮጵያውያን_ድምጽ *ትክክለኛዎቹን የአሐዱ ራዲዮ የማህበራዊ ሚዲያ ገጾች በመቀላቀል ቤተሰብ ይሁኑ!* ፌስቡክ: https://www.facebook.com/ahaduradio ድረ ገጽ፡- https://ahaduradio.com/ ዩትዩብ፦ http://shorturl.at/cknFP ቲክቶክ ፡- www.tiktok.com/@ahadutv.official ዋትስአፕ፦ whatsapp.com/channel/0029VajDfVZI1rcb05C5B22b አስተያየት እና ጥቆማ ለመስጠት በ7545 አጭር የፅሁፍ መልክት ይላኩ
Image from Ahadu Radio And Television: *በዋግኽምራ ዞን ዝቋላ ወረዳ 35 ሺሕ ዜጎች ለረሀብ መጋለጣቸው ተገለጸ*   ሰኔ 10/2017 (አሐዱ ሬዲዮ) ...

Comments