Ahadu Radio And Television
June 18, 2025 at 04:44 PM
*"እስራኤል የከፈተችው ጦርነት አላማ ኢራንን ማጥፋት ሳይሆን እስራኤልን ማዳን ነው" በኢትዮጵያ የእስራኤል አምባሳደር አቭራሃም ንጉሤ (ዶ/ር)*
👉 *"የኢራን የቴሌቪዥን ጣቢያዎች የሲቪል ተቋም ሳይሆኑ የፕሮፖጋንዳ መሳሪያ ናቸው" ብለዋል*
ሰኔ 11/2017 (አሐዱ ሬዲዮ) እስራኤል ከ6 ቀናት በፊት በኢራን ላይ በሌሊት ድንገት በከፈተችው በድሮን እና በሚሳኤል የታገዘ ወታደራዊ ጥቃት መነሻነት የተጀመረው ጦርነት ዓላማ ኢራንን ማጥፋት ሳይሆን እስራኤልን ማዳን ነው ሲሉ በኢትዮጵያ የእስራኤል አምባሳደር አቭራሃም ንጉሤ (ዶ/ር) ተናገሩ።
አምባሳደሩ ይህን ያሉት በትላንትናው ዕለት ለመገናኛ ብዙኃን ባለሙያዎች በሰጡት ጋዜጣዊ መግለጫ ነው፡፡
በተደጋጋሚ "ኢራን የኒኩሊየር እና የባለስቲክ ሚሳኤሎች ባለቤት ልትሆን አይገባም" ሲሉ የተደመጡት አምባሳደሩ፤ "እስራኤል ወደ አውዳሚ ጦርነቱ የገባቸው የህልውና አደጋ ስለተጋረጠባት ነው" ብለዋል፡፡
ጦርነቱ ከመፈንዳቱ በፊት በሁለቱ ሀገራት መካከል 60 ቀናትን የፈጀ ድርድር መካሄዱን ያስታወሱም ሲሆን፤ "ኢራን በድርድሩ ወቅት ሳይቀር እስራኤልን የማጥፋት እቅዷን ለማሳካት እንቅስቃሴ ውስጥ ነበረች" ሲሉ ከሰዋል፡፡
"እስራኤል ራሷን ከመጥፋት ለመታደግ የገባችበት ጦርነት ፍትሐዊ ነው፤ የእስራኤል ጥቃት በኢራን ሳትቀደም በፊት ቀድሞ የተሰነዘረ እንጂ ኢራንን ማጥፋትን ታሳቢ ያደረገ አይደለም" ሲሉም፤ ከጋዜጠኞች ለቀረበላቸው ጥያቄ በሰጡት ማብራሪያ ገልጸዋል፡፡
"ኢራን እስራኤልን ብቻ ሳይሆን መላው አውሮፓን ሊያወድም የሚችል የኒኩሊየር መሳሪያ ዝግጅት ላይ ነበረች" ያሉት አምባሳደሩ፤ "ኢራን አላማዋ እስራሴልን ማጥፋት እንደሆነ በግልጽ እና በተደጋጋሚ አሳውቃለች። ይህ ሁኔታም ከንግግር አልፎ ተግባራዊ እንቅስቃሴ ውስጥ ተገብቷል፡፡ የእስራኤል መንግሥትም ዜጎቹን ከጥፋት የማዳን ኃላፊነቱን ለመወጣት፤ ወደዚህ ጦርነት ለመግባት ተገዷል" ብለዋል፡፡
አምባሳደር አቭራሃም (ዶ/ር) "ኢራን እስራኤልን ማጥፋት የፈለገችበት ምክንያት ምንድን ነው?" ሲል አሐዱ ላቀረበው ጥያቄ፤ “ኢራን የኒኩሊየር ባለቤት መሆን የፈለገችው እስራኤልን ለማጥፋት እንደሆነ ግልጽ ነው፡፡ የዚህ ምክንያት ግን ለእኛም አልገባንም፡፡ የድንበር ግጭት የለንም፡፡ ከ2 ሺሕ ኪ.ሜ. ርቀት ላይ ከሚገኝ ርቀት ተነስተው ከ10 ሚልዮን የሚበልጡ ዜጎችን ከታሪካዊ ቦታቸው ላይ ማጥፋት የፈለጉበት ምክንያት ግልጽ አይደለም” የሚል ምላሽ ሰጥተዋል፡፡
እስራኤል በኢራን ላይ የከፈተችው ወታደራዊ ጦርነት ዓላማ "ራሴን ከጥፋት ለማዳን ስል ሳይቀድሙኝ በፊት የሰነዘርኩት ጥቃት ነው" ብትልም፤ ወታደራዊ ያልሆኑ እና ከኒኩሊየር እና ባለስቲክ ሚሳኤል ማብላያ ጋር ግንኙነት የሌላቸው ተቋማትም ጥቃት ሲሰነዘርባቸው ይስተዋላል፡፡
አሐዱም "እስራኤል የሲቪል ተቋማት ላይ ጥቃት የሰነዘረችው ለምንድን ነው?" ሲል አምባሳደሩን ጠይቋል፡፡
አምባሳደር አቭራሃም (ዶ/ር) በሰጡት ምላሽ፤ “የቴሌቪዥን ጣቢያው የእስራኤል የፕሮፖጋንዳ መሳሪያ እንጂ የሲቪል ተቋም አይደለም" ብለዋል፡፡
"ቴሌቪዥን ጣቢያው የኢራንን ጨካኝ መንግሥት የሚያገለግል ተቋም ነው፡፡ የፕሮፖጋንዳ መሳሪያ ነው፡፡ ይህ በመሆኑ እስራኤል የኒኩሌር ፕሮግራሙን ለማዳከም እና ለማጥፋት በምታደርገው ጥረት የቴሌቪዥን ጣቢያው የጥቃቱ ሰለባ ሊሆን ችሏል" ሲሉ አብራርተዋል፡፡
"ከ2 ሺሕ ኪ.ሜ. ርቀት ላይ እየተካሄደ የሚገኘው የሁለቱ ሀገራት ሀገር አቋራጭ ጦርነት በአፍሪካ ሀገራት ላይ የሚያሳድረው ተጽዕኖ ምንድን ነው? በሚል ለቀረበላቸው ጥያቄ ዶ/ር አቭራሃም ሲመልሱ፤ ጦርነቱ አፍሪካ ላይ ተጽዕኖ ያሳድራል የሚል እምነት እንደሌላቸውና እስራኤል የኢራን የኒኩሊየር ፕሮግራም ሙሉ ለሙሉ መውደሙን ስታረጋግጥ ጦርቱ እንደሚያበቃ ተናግረዋል።
በዳዊት አርአያ
#አሐዱ_የኢትዮጵያውያን_ድምጽ
*ትክክለኛዎቹን የአሐዱ ራዲዮ የማህበራዊ ሚዲያ ገጾች በመቀላቀል ቤተሰብ ይሁኑ!*
ፌስቡክ: https://www.facebook.com/ahaduradio
ድረ ገጽ፡- https://ahaduradio.com/
ዩትዩብ፦ http://shorturl.at/cknFP
ቲክቶክ ፡- www.tiktok.com/@ahadutv.official
ዋትስአፕ፦ whatsapp.com/channel/0029VajDfVZI1rcb05C5B22b
አስተያየት እና ጥቆማ ለመስጠት በ7545 አጭር የፅሁፍ መልክት ይላኩ