Ahadu Radio And Television
Ahadu Radio And Television
June 19, 2025 at 10:53 AM
*የኢራን ሚሳኤሎች የሶሮቃ ሆስፒታልን ጨምሮ አራት ቦታዎች ላይ ከባድ ጉዳት ማድረሳቸውን ተገለጸ* 👉 *ጥቃቱን ተከትሎ እስራኤል የኢራን አራክ ከባድ ውሃ የኒውክሌር ኃይል ማመንጫ ላይ ጥቃት ሰንዝራለች* ሰኔ 12/2017 (አሐዱ ሬዲዮ) የኢራን ሚሳኤሎች በደቡባዊ እስራኤል ቤርሼቫ ከተማ ውስጥ የሚገኘው ሶሮቃ ሆስፒታልን ጨምሮ፤ በማዕከላዊ እና በደቡብ እስራኤል በሚገኙ አራት ቦታዎች ላይ ከባድ ጉዳት ማድረሳቸው ተዘግቧል፡፡ የኢራንን ሚሳኤሎች ከሆስፒታሉ በተጨማሪ በቴል አቪቭ፣ በምስራቅ ራማት ጋን እና በደቡብ ሆሎን ላይ ጥቃት መሰንዘራቸው የተገለጸ ሲሆን፤ ጥቃቱን ተከትሎ በመላው እስራኤል የአየር ጥቃት ማስጠንቀቂያ ደውሎች ተሰምተዋል። የኢራን መንግሥት የዜና ወኪል (ኢ.አር.ኤን.ኤ) "ዛሬ የተፈጸመው የሚሳኤል ጥቃት ዋና ኢላማ በሆስፒታሉ አቅራቢያ የሚገኘው የእስራኤል ወታደራዊ ማዘዣ እና የስለላ ጣቢያ ላይ እንጂ በሆስፒታሉ ላይ እንዳልነበር" ዘግቧል፡፡ በዚህም "የጥቃቱ ዒላማ ያደረገው በጋቭ-ያም ቴክኖሎጂ ፓርክ ውስጥ የሚገኘውን የእስራኤል መከላከያ ሃይል የዕዝ እና ደህንነት ዋና መስሪያ ቤት ላይ ነው" ብሏል፡፡ የእስራኤል ብሔራዊ የድንገተኛ አደጋ የሕይወት አድን ብሔራዊ አገልግሎት እንደገለጸው፤ ኢራን በሆስፒታሉ ላይ በሰነዘረችው የሚሳኤል ጥቃት የተጎዱ ሰዎች ቁጥር አሁን 47 የደረሰ ሲሆን፤ በሦስት ሰዎች ላይ ከባድ ጉዳት እንዲሁም በሁለት መጠነኛ ጉዳት ደርሷል። "ተጨማሪ 18 ሰዎች ወደ መጠለያ ጣቢያ በማቅናት ላይ ሳሉ ቆስለዋል" ሲል ብሔራዊ አገልግሎቱ ገልጿል። ይህን ተከትሎም የእስራኤል ጦር ተዋጊ ጄቶች ዛሬ ማለዳ በአራክ የከባድ ውሃ የኒውክሌር ኃይል ማመንጫን ጨምሮ፤ በደርዘን የሚቆጠሩ የኢራን ጣቢያዎችን በአንድ ጀምበር መምታታቸውን እስራኤል አስታውቃለች፡፡ የተዋጊ ጄቶቹ ጥቃት "የኑክሌር የጦር መሳሪያ ለመስራት በሚውለው ፕሉቶኒየም ምርት ውስጥ ቁልፍ አካል የሆነውን የ"ሬአክተር መዋቅር" ላይ ያነጣጠረ መሆኑንም ገልጻለች፡፡ ቀደም ሲል የእስራኤል ጦር በሪአክተሩ አካባቢ የሚኖሩ ሰዎች በአስቸኳይ እንዲለቁ ማሳሰቢያ መስጠቱ ይታወሳል፡፡ በተጨማሪም ከመሬት በታች በሚገኘው "ናታንዝ የኑክሌር ጦር መሳሪያ ልማት ጣቢያ" እና ለባለስቲክ ሚሳኤሎች የሚያስፈልጉ አካላትን የሚያመርቱ በርካታ ፋብሪካዎችን ላይ ጥቃት መሰንዘሯን እስራኤል ተናግራለች፡፡ የእስራኤል ባለስልጣናት በሶሮቃ ሆስፒታል ላይ በደረሰው ጥቃት ቁጣቸውን በመግለጽ ላይ የሚገኙ ሲሆን፤ ጠቅላይ ሚኒስትር ቤኒያሚን ኔታኒያሁ "ኢራን በእስራኤል ላይ ለፈጸመችው ጥቃት ዋጋ ትከፍላለች" ሲሉ በኤክስ ገጻቸው ባስተላለፉት መልዕክት ገልጸዋል። የእስራኤል ፕሬዝዳንት አይዛክ ሄርዞግ በበኩላቸው፤ "በሆስፒታሉ ለአደጋ የተጋለጡ ሕመምተኞች ኢራን በእስራኤል ሲቪሎች ላይ ያደረሰችው የሚሳኤል ጥቃት ኢላማዎች ናቸው" ብለዋል። የሀገሪቱ ምክትል የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ሻረን ሃስኬል ደግሞ፤ "በሶሮቃ ሆስፒታል ላይ የተሰነዘረው ጥቃት ሆን ተብሎ ሲቪል ዜጎችን ኢላማ በማድረግ የተሰነዘረ ነው" ያሉ ሲሆን፤ "ይህንን በንጹሃን ላይ ያነጣጠረ ጥቃት ዓለም ማወቅ እና ማውገዝ አለበት" ሲሉ ተናግረዋል፡፡ የእስራኤል የፖለቲካ ተንታኝ ኦሪ ጎልድበርግ በእስራኤል ውስጥ መንግሥታቸው "ነገሮችን በቁጥጥር ሥር እያዋለ ነው" የሚል ምላሽ ቢሰጥም፤ "ነገር ግን የኢራን የቅርብ ጊዜ ጥቃቶች በሀገሪቱ ላይ ከፍተኛ ጉዳት እያደረሱ ነው" ብለዋል፡፡ ይህ በሁለቱ ሀገራት መካከል እየተደረገ ያለው ጦርነት እየተባባሰ ባለበት በዚህ ወቅት የአሜሪካው ፕሬዝዳንት ዶናልድ ትራምፕ በግጭት ውስጥ የአሜሪካ ወታደራዊ ጣልቃገብነት ላይ ያላቸውን አማራጮች እያዩ እንደሚገኙ አስታውቀዋል፡፡ ቀደም ሲል የኢራኑ መንፈሳዊ መሪ አያቶላህ አሊ ካሜኔ "በግዛቷ ላይ የሚደርስ ማንኛውም ጥቃት ከባድ የማይጠገን መዘዝ ያስከትላል" ሲሉ አሜሪካን ማስጠንቀቃቸው ይታወሳል። እስራኤል በኢራን ላይ ባደረሰችው ጥቃት የሞቱት ሰዎች ቁጥር ከ240 በላይ ሲሆን፤ ከእነዚህም መካከል 70 ሴቶች እና ሕጻናት እንደሚገኙበት መገናኛ ብዙኃኑ ዘግበዋል። እንዲሁም ኢራን በእስራኤል ላይ ባደረሰችው ጥቃት 24 ሰዎች መገደላቸው ተገልጿል። በእዮብ ውብነህ #አሐዱ_የኢትዮጵያውያን_ድምጽ *ትክክለኛዎቹን የአሐዱ ራዲዮ የማህበራዊ ሚዲያ ገጾች በመቀላቀል ቤተሰብ ይሁኑ!* ፌስቡክ: https://www.facebook.com/ahaduradio ድረ ገጽ፡- https://ahaduradio.com/ ዩትዩብ፦ http://shorturl.at/cknFP ቲክቶክ ፡- www.tiktok.com/@ahadutv.official ዋትስአፕ፦ whatsapp.com/channel/0029VajDfVZI1rcb05C5B22b አስተያየት እና ጥቆማ ለመስጠት በ7545 አጭር የፅሁፍ መልክት ይላኩ
Image from Ahadu Radio And Television: *የኢራን ሚሳኤሎች የሶሮቃ ሆስፒታልን ጨምሮ አራት ቦታዎች ላይ ከባድ ጉዳት ማድረሳቸውን ተገለጸ*   👉 *ጥቃ...

Comments