Ahadu Radio And Television
Ahadu Radio And Television
June 19, 2025 at 04:07 PM
*"ኢራን ሉዓላዊነቷንና ሕዝቧን ለመጠበቅ ሙሉ አቅሟን ትጠቀማለች" በኢትዮጵያ የኢራን አምባሳደር አሊ አክባር ረዛኢ* ሰኔ 12/2017 (አሐዱ ሬዲዮ) ከባለፈው ሳምንት አርብ ጀምሮ የእስራኤል መንግሥት በኢራን እስላማዊ ሪፐብሊክ ግዛት ላይ የሚፈጽመውን ጥቃት ለመመከት እንዲሁም፤ ሉዓላዊነቷንና ሕዝቧን በሙሉ አቅሟ ለመጠበቅ ኢራን ዝግጁ ናት ሲሉ በኢትዮጵያ የኢራን እስላማዊ ሪፐብሊክ አምባሳደር አሊ አክባር ረዛኢ ተናግረዋል፡፡ አምባሳደሩ በዛሬው ዕለት በሰጡት መግለጫ፤ "ኢራን ከእስራኤል ጥቃት ራሷን የመከላከል ተፈጥሯዊ መብቷን ትጠቀማለች" በማለት ተናግረዋል፡፡ "እሰራኤል የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ቻርተርን አንቀፅ 2 (4)ን በመጣስ በሉዓላዊቷ የኢራን እስላማዊ ሪፐብሊክ ላይ ጥቃት ፈፅማለች" ያሉት አምባሳድር ረዛኢ፤ "ኢራንም በመንግሥታቱ ድርጅት ቻርተር አንቀጽ 52 መሰረት ራሷን የመከላከል መብት አላት" ሲሉ ገልጸዋል፡፡ "በዚህም እኛ ጦርነቱን አልጀመርነውም፤ ነገር ግን ሕዝባችንና ሀገራችንን ሙሉ አቅማችንን በመጠቀም ለመጠበቅ ዝግጁ ነን" ብለዋል፡፡ አምባሳደር ረዛኢ አክለውም፤ "የእስራኤል ፅዮናውያን አገዛዝ የኢራንን ሰላማዊ የኒውክሌር ተቋማትን የጥቃት ኢላማ አድርጓል" ያሉ ሲሆን፤ "በኒውክሌር ተቋማት ላይ ጥቃት መፈጸም በአካባቢ ላይ የሚያደርሰው ጉዳትም ለሁሉም ግልጽ ነው" ሲሉ አብራርተዋል፡፡ ከዚህ ባሻገርም የዓለም አቀፉ የአቶሚክ ኢነርጂ ኤጀንሲ ኃላፊ ዛሬ ባደረጉት ፍተሻ፤ እስራኤል 'ኢራን የኒውክሌር ቦንብ ልትሰራ ነው' ስትል ያቀረበችውን ክስ ሀሰት እንደሆነም ማረጋገጣቸውን ለአሐዱ ተናግረዋል፡፡ አምባሳደር ረዛኢ በመግለጫቸው "ሆስፒታሎች፣ ብሄራዊ የሬድዮና ቴሌቪዥን ሕንጻ፣ የመኖሪያ ቤቶችና ንጹኃን በእስራኤል ጥቃቶች ኢላማ ተደርገዋል" ያሉ ሲሆን፤ ይህም የሦስት ወር ሕጻናትንና ነፍሰ ጡር ሴቶችን ጨምሮ በርካቶች ተገድለዋል ብለዋል፡፡ በተጨማሪም "የእስራኤል አገዛዝ ጥቃት የሰነዘረው ኢራንና አሜሪካ በኒውክሌር ጉዳይ ላይ ለአምስት ዙር ያክል ድርድር እያደረጉ ባለበት ወቅት ነው" ሲሉ የተናገሩት አምባሳደሩ፤ "ይህም ማን ሰላም ፈላጊ ማን ጸብ አጫሪ ነው የሚለውን በግልጽ ያሳያል" ሲሉ ጠቁመዋል፡፡ በታሪኩ ጋሹ #አሐዱ_የኢትዮጵያውያን_ድምጽ *ትክክለኛዎቹን የአሐዱ ራዲዮ የማህበራዊ ሚዲያ ገጾች በመቀላቀል ቤተሰብ ይሁኑ!* ፌስቡክ: https://www.facebook.com/ahaduradio ድረ ገጽ፡- https://ahaduradio.com/ ዩትዩብ፦ http://shorturl.at/cknFP ቲክቶክ ፡- www.tiktok.com/@ahadutv.official ዋትስአፕ፦ whatsapp.com/channel/0029VajDfVZI1rcb05C5B22b አስተያየት እና ጥቆማ ለመስጠት በ7545 አጭር የፅሁፍ መልክት ይላኩ
Image from Ahadu Radio And Television: *"ኢራን ሉዓላዊነቷንና ሕዝቧን ለመጠበቅ ሙሉ አቅሟን ትጠቀማለች" በኢትዮጵያ የኢራን አምባሳደር አሊ አክባር ረ...

Comments