
Ahadu Radio And Television
June 20, 2025 at 10:12 AM
*ኢሰመጉ የተደረገብኝ ዕገዳ በሥራዬ ላይ ተፅዕኖ አሳድሯል ሲል ገለጸ*
ሰኔ 13/2017 (አሐዱ ሬዲዮ) በኢትዮጵያ ሲቪል ማህበረሰብ ድርጅቶች ባለስልጣን ተጥሎበት የነበረው ግዜያዊ ዕገዳ፤ አሁን በሚሰራው ሥራ ላይ ተግዳሮት እየሆነበት እንደሚገኝ የኢትዮጵያ ሰብዓዊ መብቶች ጉባኤ (ኢሰመጉ) አስታውቋል፡፡
የሲቪል ማህበረሰብ ድርጅቶች ባለስልጣን በዚህ ዓመት ኢሰመጉን ጨምሮ ሌሎች 5 በሰብዓዊ መብቶች ላይ የሚሠሩ የሲቪል ማህበረሰብ ድርጅቶች ላይ፤ "ከተቋቋሙበት ዓላማ ውጪ ሲንቀሳቀሱ አግኝቻለው" በማለት ዕግድ መጣሉ ይታወሳል፡፡
ጉባኤው ከባለስልጣኑ ከፍተኛ የሥራ ሃላፊዎች ጋር ባደረው ውይይት መሠረት፤ ከካቲት 24 ቀን 2017 ዓ.ም. ጀምሮ በሲቪል ማህበረሰብ ድርጅቶቹ ላይ ተጥሎ የነበረው ዕግድ በማስጠንቀቂያ መነሳቱ ተገልጿል።
በዚህም የሰብዓዊ መብቶች ጉባኤው በተደጋጋሚ በአመራሮቹና በሠራተኞቹ ላይ ዛቻ እና ማስፈራሪያ የደረሰበት መሆኑ የገለጸ ሲሆን፤ የቀድሞ የጉባኤው ዋና ዳይሬክተር አቶ ዳን ይርጋ በዚህ ምክንያት ከሀገር መሰደዳቸውም መገለጹ አይዘነጋም፡፡
የአሁኑ የጉባኤው አዲሱ ዋና ዳይሬክተር ተስፋዬ ገመቹ አሁን ላይ ከባለስልጣን መስሪያ ቤቱ ጋር በመነጋገር ወደ ሥራ መገባቱን የገለጹ ሲሆን፤ ነገር ግን ቀደም ብሎ ተጥሎበት የነበረው እገዳ በሥራው ላይ ከፍተኛ ተፅዕኖ እንዳሳደረበት ተናግረዋል፡፡
መታገዱም ብቻ ሳይሆን ዕግዱ የተነሳበት አካሄድም በተመሳሳይ ከፍተኛ የሆነ ጫና እንዳሳደረ ያነሱት ዋና ዳይሬክተሩ፤ "ኢሰመጉ የተፈረጀበት እና ዕግዱ የተነሳበት አካሄድ ከከፍተኛ ማስጠንቀቂያ ጋር ተደርጎ መነሳቱ ተፅዕኖው እንዲባበስ አድርጓል" ብለዋል፡፡
"የትኛውን ሥራ ስንሰራ ጥፋት ተብሎ እንደምንጠየቅ ግልፅ አይደለም" ሲሉ ለአሐዱ የተናገሩት ዋና ዳይሬክተሩ ተስፋዬ ገመቹ፤ ጉባኤው ግን ከዕግዱ በፊትም ሆነ በኃላ ሕግን አክብሮ እየሰራ መሆኑን ገልጸዋል፡፡
የኢትዮጵያ ሰብዓዊ መብቶች ጉባኤ (ኢሰመጉ) በተደጋጋሚ ጊዜ የተለያ ሪፖርቶችን በሰብዓዊ መብት አያያዞች ላይ በማውጣት ትኩረት እንዲደረግባቸው የማሳሰብ ሥራ የሚሰራ ተቋም መሆኑ የሚታወቅ ነው።
በአቤል ደጀኔ
#አሐዱ_የኢትዮጵያውያን_ድምጽ
*ትክክለኛዎቹን የአሐዱ ራዲዮ የማህበራዊ ሚዲያ ገጾች በመቀላቀል ቤተሰብ ይሁኑ!*
ፌስቡክ: https://www.facebook.com/ahaduradio
ድረ ገጽ፡- https://ahaduradio.com/
ዩትዩብ፦ http://shorturl.at/cknFP
ቲክቶክ ፡- www.tiktok.com/@ahadutv.official
ዋትስአፕ፦ whatsapp.com/channel/0029VajDfVZI1rcb05C5B22b
አስተያየት እና ጥቆማ ለመስጠት በ7545 አጭር የፅሁፍ መልክት ይላኩ
