
Ahadu Radio And Television
June 20, 2025 at 05:28 PM
*በበጀቱ ዓመቱ ወደ ሀገር ይገባል ከተባለው የዘይት ምርት ውስጥ ከ65 ሚሊየን ሊትር በላይ የሚሆነው መዘግየቱን ተገለጸ*
ሰኔ 13/2017 (አሐዱ ሬዲዮ) በ2017 በጀት ዓመት ወደ ሀገር ውስጥ ይገባል ከተባለው የዘይት ምርት ውስጥ፤ ከ65 ሚሊየን ሊትር በላይ የሚሆነው መዘግየቱን የንግድና ቀጣናዊ ትስስር ሚኒስቴር አስታውቋል።
6ኛው የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት 4ኛ ዓመት የሥራ ዘመን 38ኛ መደበኛ ስብሰባ በትናንትናው ዕለት የተካሄደ ሲሆን፤ በመደበኛ ጉባዔ ላይም የንግድና ቀጠናዊ ትስስር ሚኒስቴር የ2017 በጀት ዓመት የ11 ወራት የዕቅድ አፈጻጸም ሪፖርት ተደምጧል።
በዚህም የንግድና ቀጠናዊ ትስስር ሚኒስቴር ሚኒስትር ዶ/ር ካሳሁን ጎፌ የ11 ወራት ሪፖርትን አቅርበዋል።
በሪፖርቱም "በተለይም የስኳርና ዘይት አቅርቦትን ከልማት ድርጅቶች ጋር በመሆን በገበያ ውስጥ ያለውን ፍላጎት በማሟላት የዋጋ ንረትን መቆጣጠር ተችሏል" ሲሉ ገልጸዋል።
የስኳር ምርትን ለክልሎችና ከተማ አስተዳደሮች ለማሰራጨት አንድ ሚሊየን 320 ሺሕ 160 ኩንታል ስኳር መቅረቡን አንስተዋል።
እንዲሁም የዘይት ተደራሽነትን ለማስፋት መንግሥት በፈቀደው የውጭ ምንዛሬ በመጠቀም 121 ሚሊየን ሊትር የምግብ ዘይት ለማቅረብ ታቅዶ፤ ከመንግሥት የልማት ድርጅቶች ግዢ የተፈጸመው 55 ሚሊየን 960 ሺሕ ሊትር በኮታ ክፍፍል መሰረት መሠራጨቱን ተናግረዋል።
"ነገር ግን 65 ሚሊየን 340 ሺህ ሊትር ዘይት አለም አቀፍ ጨረታውን ያሸነፉ አቅራቢዎች በገቡት ስምምነት መሰረት ለመንግስት ልማት ድርጅቶች በወቅቱ ባለማቅረባቸው ሊዘገይ ችሏል" ሲሉ ገልጸዋል። ይህንንም ለማስተካከል የክትትል ሥራ እንደሚሰራ አንስተዋል።
እንዲሁም በበጀት ዓመቱ መጀመሪያ ወራት የማክሮ ኢኮኖሚ ማሻሻያ መደረጉን ተከትሎ፤ የሸማቹን ማህበረሰብ ጥቅም የሚጎዳ የዋጋ ጭማሪ በስፋት የታየበት ወቅት መሆኑን ጠቁመዋል።
"ችግሩን ለመከላከል የማክሮ ኢኮኖሚ ማሻሻያና የንግድ መዋቅሩን ሂደት ግንዛቤ ለመስጠት ተሞክሯል" ብለዋል።
ለዚህም ሕገ-ወጥ ተግባራትን ሲፈጽሙ በተገኙ 110 ሺሕ 577 የንግድ ድርጅቶችና ነጋዴዎች ላይ አስተዳደራዊ እርምጃዎች መወሰዳቸውን ገልጸዋል።
በተጨማሪም ነዳጅን ጨምሮ ከሕገ-ወጥነት የተወረሱ ምርቶች ሽያጭ እና በሕገ-ወጦች ላይ በክልሎችና በፌደራል ደረጃ 221 ሚሊየን ብር ገቢ ለመንግሥት ገቢ መደረጉን ሚኒስትሩ ገልጸዋል።
በፍርቱና ወልደአብ
#አሐዱ_የኢትዮጵያውያን_ድምጽ
*ትክክለኛዎቹን የአሐዱ ራዲዮ የማህበራዊ ሚዲያ ገጾች በመቀላቀል ቤተሰብ ይሁኑ!*
ፌስቡክ: https://www.facebook.com/ahaduradio
ድረ ገጽ፡- https://ahaduradio.com/
ዩትዩብ፦ http://shorturl.at/cknFP
ቲክቶክ ፡- www.tiktok.com/@ahadutv.official
ዋትስአፕ፦ whatsapp.com/channel/0029VajDfVZI1rcb05C5B22b
አስተያየት እና ጥቆማ ለመስጠት በ7545 አጭር የፅሁፍ መልክት ይላኩ
