Ahadu Radio And Television
Ahadu Radio And Television
June 20, 2025 at 05:29 PM
*ኢራን አዲስ የሚሳኤል ጥቃት እስራኤል ላይ መሰንዘሯ ተገለጸ* 👉 *የፈረንሳይ፣ የጀርመን፣ የዩናይትድ ኪንግደም እና የአውሮፓ ሕብረት ከፍተኛ ዲፕሎማቶች በዛሬው ዕለት ከኢራን ጋር ይወያያሉ* ሰኔ 13/2017 (አሐዱ ሬዲዮ) ኢራን በዛሬው ዕለት በሰሜናዊ፣ መካከለኛው እና ደቡባዊ እስራኤል አዲስ የሚሳኤል ጥቃት መሰንዘሯን የእስራኤል መከላከያ ኃይል አስታውቋል። ኢራን በሰሜናዊ እስራኤል ሀይፋ ግዛት ከሰዓትት በፊት የሚሳኤል ጥቃት ማድረሷ የተገለጸ ሲሆን፤ ጥቃቱን ተከትሎ በመላው እስራኤል የአየር ጥቃት ማስጠንቀቂያ ደውሎች ተሰምተዋል፡፡ ነዋሪዎችም "የተከለሉ ስፍራዎች ውስጥ ገብተው እስከሚቀጥለው ማስታወቂያ ድረስ እዚያው እንዲቆዩ" ትዕዛዝ መተላለፉም ተነግሯል። በዛሬው የኢራን ጥቃት ከ20 በላይ ሚሳይሎች ወደ እስራኤል መወንጨፋቸውን የእስራኤል መከላከያ ኃይል የገለጸ ሲሆን፤ በሀይፋ ግዛት ከባድ ጉዳት መድረሱን አስታውቋል። በሃይፋ ግዛት የሚኖሩ ነዋሪዎች ከኢራን አዲስ የሚሳኤል ጥቃት ለማምለጥ ከገበያ ማዕከል በታች ወደሚገኝ የመሬት ውስጥ የመኪና ማቆሚያ ስፍራ ሲሯሯጡ መታየታቸውንም የሲኤንኤን ዘገባ አመላክቷል፡፡ የእስራኤል መገናኛ ብዙሃን እንደዘገቡት ከሆነ የኢራን ሚሳይሎች ከሃይፋ በተጨማሪ በጉሽ ዳን ግዛት፣ በቴል አቪቭ እና ቤርሳቤህ ላይ ያረፉ ሲሆን፤ በሁለቱም በቴል አቪቭ እና በእየሩሳሌም ከተሞች ከፍተኛ ፍንዳታዎች ተሰምተዋል። በጥቃቱም ቢያንስ 17 ሰዎች መቁሰላቸውን የእስራኤል የጤና እና የድንገተኛ አደጋ ባለስልጣናት ሲገልጹ፤ ጉዳት ከደረሰባቸው ሰዎች ውስጥ የ16 ዓመት ታዳጊን ጨምሮ ቢያንስ ሦስቱ በከባድ ቆስለዋል ብለዋል፡፡ የኢራን አብዮታዊ ዘብ ጥቃቱ "17ኛው ኦፕሬሽን ትሩል ፕሮሚዝ 3" መሆኑን የገለጸ ሲሆን፤ የተቀናጀ ረጅም ርቀት እና ከባድ ሚሳኤሎችን ያካተተ መሆኑን አስታውቋል። የአብዮታዊ ዘብ ቃል አቀባይ እንደተናገሩት ጥቃቱ ያነጣጠረው፤ "ወታደራዊ ቦታዎችን፣ የጦር መሣሪያ ኢንዱስትሪዎች እና የማዘዣ ማዕከላት" ላይ ነው። ስምንተኛ ቀኑን የያዘው የኢራን እና እስራኤል ግጭት ተባብሶ የቀጠለ ሲሆን፤ የፈረንሳይ፣ የጀርመን፣ የዩናይትድ ኪንግደም እና የአውሮፓ ሕብረት ከፍተኛ ዲፕሎማቶች ግጭቱን በውይይት ለማስቆም፤ ከኢራን የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር አባስ አራግቺ ጋር በስዊዘርላንድ ጄኔቫ በዛሬው ዕለት ይገናኛሉ ተብሏል፡፡ በዚህም ውይይት ላይ የፈረንሳዩ ፕሬዚዳንት ኢማኑኤል ማክሮን ከእስራኤል ጋር ያለውን ግጭት ማስቆም የሚያስችል የዲፕሎማሲ ፕሮፖዛል ለኢራን እንደሚያቀርቡ የገለጹ ሲሆን፤ ፕሮፖዛሉ በአራት ዋና ዋና ክፎሎች የተዋቀረ መሆኑን አስታውቀዋል፡፡ በዚህም በኢራን ላይ የዓለም አቀፉ የአቶሚክ ኤነርጂ ኤጀንሲ (አይ.ኤ.ኢ.ኤ) ሥራውን እንዲጀምር እና የዩራኒየምን ማበልጸግ ሥራ ወደ ዜሮ ማሸጋገር፣ የኢራንን የባለስቲክ ሚሳኤል እንቅስቃሴ መቆጣጠር፣ ኢራን በቀጣናው ላሉ ተዋጊ ቡድኖች የምታደርገውን የገንዘብ ድጋፍ አስመልክቶ እንዲሁም በኢራን ውስጥ ያሉ ታጋቾችን ነጻ ማውጣት ቅድሚያ እንዲሰጠው የሚጠይቅ መሆኑን ማክሮን አስረድተዋል፡፡ የማክሮን የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ዣን ኖኤል ባሮት እና የጀርመን እና የብሪታንያ ባልደረቦቻቸው "የተሟላ ድርድር፣ ዲፕሎማሲያዊ እና ቴክኒካዊ አቅርቦት" ላይ ያተኮሩ የድርድት ሃሳቦችን ለኢራኑ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር አባስ አራግቺ እንደሚያቀርቡም ተናግረዋል፡፡ የኢራን የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር በበኩላቸው ኢራን በእስራኤል ያልተጠበቀ ጥቃት የተፈጸመባት፤ "ከአሜሪካ ጋር የኒውክሌር አቅምን አስመልክቶ ተስፋ ሰጪ ዲፕሎማሲያዊ ሂደት ላይ በነበረችበት ወቅት" ብለዋል፡፡ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሩ ይህን ያሉት በተባበሩት መንግሥታት ድርጅት የሰብዓዊ መብቶች ምክር ቤት በጄኔቫ በግጭቱ ዙሪያ በመከረበት ስብሰባ ላይ ሲሆን፤ እስራኤል በአገራቸው ላይ ያደረሰችው ጥቃት "ለሰው ልጅ ስልጣኔ ታሪካዊ ወቅት ነው" በማለት፤ አገራት ለዓለም አቀፍ ሕግ መቆም እንዳለባቸው ማሳሰባቸውን ቢቢሲ ዘግቧል። አባስ አራግቺ እስራኤል በአገራቸው ላይ የፈጸመችውን ድንገተኛ ጥቃት፤ "የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ቻርተርን የሚጥስ እንዲሁም ይህ ምክር ቤት የቆመበትን መርህ የሚጻረር ነው" ሲሉም መግለጻቸው ተነግሯል። የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሩ እስራኤል ጥቃቷን እስካላቆመች ድረስ ሀገራቸው ከአሜሪካ ጋር ለድርድር እንደማትቀመጥ መናገራቸውም ተዘግቧል፡፡ በእዮብ ውብነህ #አሐዱ_የኢትዮጵያውያን_ድምጽ *ትክክለኛዎቹን የአሐዱ ራዲዮ የማህበራዊ ሚዲያ ገጾች በመቀላቀል ቤተሰብ ይሁኑ!* ፌስቡክ: https://www.facebook.com/ahaduradio ድረ ገጽ፡- https://ahaduradio.com/ ዩትዩብ፦ http://shorturl.at/cknFP ቲክቶክ ፡- www.tiktok.com/@ahadutv.official ዋትስአፕ፦ whatsapp.com/channel/0029VajDfVZI1rcb05C5B22b አስተያየት እና ጥቆማ ለመስጠት በ7545 አጭር የፅሁፍ መልክት ይላኩ
Image from Ahadu Radio And Television: *ኢራን አዲስ የሚሳኤል ጥቃት እስራኤል ላይ መሰንዘሯ ተገለጸ*   👉 *የፈረንሳይ፣ የጀርመን፣ የዩናይትድ ኪን...

Comments