Ahadu Radio And Television
Ahadu Radio And Television
June 21, 2025 at 10:44 AM
*የፕላስቲክ (ፌስታል) ምርትን ለመከልከል የጸደቀው አዋጅ ግልጽነት የጎደለው ነው ሲል የፕላስቲክና ጎማ የአምራች ማህበር አስታወቀ* 👉 *ዘርፉ በአጠቃላይ አገራዊ ምርት ገቢ ውስጥ የ59 ቢሊዮን ብር አስተዋጽኦ እንዳለው ተገልጿል* ሰኔ 14/2017 (አሐዱ ሬዲዮ) በቅርቡ በሕዝብ ተወካዮች ም/ቤት የጸደቀውንና በተለይ አንድ ጊዜ ብቻ ጥቅም ላይ የሚውለውን የፕላስቲክ ከረጢት (ስስ ፌስታል) ማምረትና ለገበያ ማቅረብን በሚከለክለው አዲስ አዋጅ፤ ግልጽነት የጎደለው ነው ሲል የፕላስቲክና ጎማ የአምራች ማህበር አስታውቋል። የማኅበሩ አባልና ጊዜያዊ ኮሚቴ ሰብሳቢ አቶ በረከት ገብረህይወት ለጋዜጠኞች በሰጡት ማብራሪያ፤ "አዋጁ የግልጽነት ችግር ያለበትና በዘርፉ የተሰማሩ ባለሃብቶችና ሠራተኞችን ለኪሳራ የሚዳርግ ነው" ብለዋል። አክለውም፤ አዋጁ በርካታ የፋብሪካ ባለቤቶችና ሠራተኞች ላይ ከፍተኛ የሕልውና ሥጋት መፍጠሩን አስረድተዋል። የአዋጁ የአተረጓጎም ችግር ያለበት እና ግልጽነት የጎደለው መሆኑን የገለጹት ሰብሳቢው፤ በተለይ ይህ አዋጅ ከመጽደቁ በፊት በማርቀቅ ሂደት ላይ እያለ ባለ ድርሻ አካላት ያልተወያዩበትና ሃሳባቸውን ያልሰጡበት መሆኑን ገልጸዋል። ይህም በአዋጁ ላይ ለሚታየው የግልጽነት ችግር ጉልህ አስተዋጽኦ ማድረጉን በመግለጽ፤ "ከጥቅም ውጭ የሆኑ ፌስታሎች በድጋሚ እየታደሱ ለሌላ አገልግሎት እየሰጡ መሆኑም አዋጁ በአተረጓጎም ደረጃ ችግር ያለበት መሆኑን የሚያሳይ ነው" ብለዋል፡፡ አዋጁ "ከአንድ ጊዜ በላይ ጥቅም የማይሰጡ" ሲል በአተረጓጎም የሚጣረስበት ምክንያት፤ "ከተለያዩ ቦታዎች የወዳደቁ (ከጥቅም ውጭ የሆኑ) ፌስታሎችና ጎማዎች መልሰው እንዲታደሱ በማድረግ እየተሰራ የሚገኘውን ሥራ ታሳቢ ያላደረገ መሆኑን የሚያሳይ በመሆኑን ነው" ሲሉም ተናግረዋል። በአዲሱ አዋጅ በአዲስ አበባ ከተማ ብቻ ከ800 በላይ በፕላስቲክ ምርት ላይ የተሰማሩ አምራቾችን ስጋት ላይ የጣለ መሆኑን የገለጹት የማህበሩ ሰብሳቢ፤ 268 ሺሕ የሚሆኑ ሠራተኞች ከሥራ ገበታቸው የሚያፈናቅል መሆኑን አስረድተዋል። በተጨማሪም ዘርፉ በአጠቃላይ አገራዊ ምርት ውስጥ የ59 ቢሊዮን ብር አስተዋጽኦ እንዳለው የገለጹ ሲሆን፤ "በመሆኑም መንግሥት እነዚህን ጉዳዮች አዋጁ ተግባራዊ ከመደረጉ አስቀድሞ ሊያጤነው ይገባል" ብለዋል። አዋጁ ከወጣበት ወይንም በነጋሪት ጋዜጣ ከወጣበት ቀን ጀምሮ በ6 ወራት ጊዜ ውስጥ ተፈጻሚ እንደሚሆን መገለጹን በማንሳትም፤ የተቀመጠው የሽግግር ጊዜ በቂ አለመሆኑን ተናግረዋል፡፡ አክለውም ሌሎች አገራት ከ3 ዓመት ያነሰ የሽግግር ጊዜ እንዳላስቀመጡ አስታውቀዋል። የኢትዮጵያ ፕላስቲክና ጎማ አምራች ድርጅቶች ከጥቅም ውጭ የነበሩ የፕላስቲክ ወይንም ፌስታል መልሰው ጥቅም ላይ እንዲውሉ ከማድረግ በተጨማሪ፤ በርካታ ወጣቶች የሥራ ዕድል እዲያገኙ አድርጓል ተብሏል፡፡ ስለሆነም "የፕላስቲክ አምራቾች ደረጃውን የጠበቀ ምርት እንዲያመርቱ ማድረግ እንጂ፤ ከዘርፉ እንዲወጡ ሊደረግ አይገባም" ሲል ማህበሩ አሳስቧል። በአለምነው ሹሙ #አሐዱ_የኢትዮጵያውያን_ድምጽ *ትክክለኛዎቹን የአሐዱ ራዲዮ የማህበራዊ ሚዲያ ገጾች በመቀላቀል ቤተሰብ ይሁኑ!* ፌስቡክ: https://www.facebook.com/ahaduradio ድረ ገጽ፡- https://ahaduradio.com/ ዩትዩብ፦ http://shorturl.at/cknFP ቲክቶክ ፡- www.tiktok.com/@ahadutv.official ዋትስአፕ፦ whatsapp.com/channel/0029VajDfVZI1rcb05C5B22b አስተያየት እና ጥቆማ ለመስጠት በ7545 አጭር የፅሁፍ መልክት ይላኩ
Image from Ahadu Radio And Television: *የፕላስቲክ (ፌስታል) ምርትን ለመከልከል የጸደቀው አዋጅ ግልጽነት የጎደለው ነው ሲል የፕላስቲክና ጎማ የአምራ...

Comments