
Ahadu Radio And Television
June 21, 2025 at 10:49 AM
*ያለ እድሜያቸው ከሚያረግዙ ሴቶች መካከል 40 በመቶ የሚሆኑት ባለትዳሮች መሆናቸው ተገለጸ*
ሰኔ 14/2017 (አሐዱ ሬዲዮ) በኢትዮጵያ ከሚፈጠሩ የልጅነት እርግዝናዎች መካከል 40 በመቶ ያክሉ እድሜያቸው ከ18 ዓመት በታች የሆነ እና በትዳር ውስጥ የሚገኙ ሴቶች መሆናቸውን የጤና ሚኒስቴር አስታውቋል።
አብዛኞቹ ያለ እድሜያቸው የሚያረግዙ ሴቶች በገጠራማው የኢትዮጵያ ክፍል የሚገኙ በመሆናቸው የግንዛቤ እጥረት መኖሩን ያነሱት በጤና ሚኒስቴር የስነ-ተዋልዶ ጤና፣ የቤተሰብ እቅድ፣ የአፍላ ወጣቶችና ወጣቶች ባለሙያ ዶክተር ታደለ ከበደ ናቸው።
በ2016 ዓ.ም. በተካሄደው የኢትዮጵያ ሥነ-ሕዝብ ጥናት መሠረት፤ በልጅነታቸው ለእርግዝና ከተጋለጡ ሴት ሕጻናት እና ታዳጊዎች መካከል 40 በመቶ የሚሆኑት በጋብቻ ውስጥ የሚገኙ ስለመሆናቸው ተናግረዋል።
"እድሜያቸው ሳይደርስ በማርገዛቸው ምክንያት ከፊስቱላህ ጀምሮ ለተለያየ አካላዊ ጉዳት ብሎም እስከ ሞት ለሚያደርስ ችግር ይጋለጣሉ" ያሉት ባለሙያው፤ ከወላጆች በተጨማሪ የሚወለዱት ሕጻናት ላይም የተለያየ የጤና ችግር ሊከሰትባቸው እንደሚችል ጠቁመዋል፡፡
በዚህም መሠረት ትምህርት ቤቶችን ጨምሮ በተለያየ ሕይወት ላይ የሚገኙትን ሴቶች ከያለእድሜ ጋብቻ እና እርግዝና ጋር በተያያዘ የተለያየ ስልጠና እንደሚሰጥ የገለጹ ሲሆን፤ "የጤና እክል በሚያጋጥማቸው ጊዜም አገልግሎት እንዲያገኙ ይደረጋል" ብለዋል።
የልጅነት እርግዝናን ለመከላከልም ከሴቶችና ማኅበራዊ ጉዳይ ሚኒስቴር፣ ከትምህርት ሚኒስቴር እንዲሁም ከፕላንና ልማት ሚኒስቴር ጋር በጋራ በመሆን በቅርብ ጊዜ ፍኖተካርታ ስለመዘጋጀቱ ገልጸዋል።
ያለእድሜ ጋብቻ እንዲቀር ለማድረግም በጤና ሚኒስቴር በኩል ያለውን አስከፊነትና የሚያመጣውን ችግር በተመለከተ መረጃ እና የጤና አገልግሎት በመስጠት እንደሚሰራ ገልጸው፤ ከፍትሕ አካላትም ሕጉን ከማስጠበቅ አንፃር በጋራ እንደሚሰራበት ተናግረዋል።
አክለውም ያለ እድሜ ጋብቻን እና እሱን ተከትሎ በሴት ልጆች ላይ የሚመጣውን ችግር ለመቅረፍ ሁሉም አካል የበኩሉን ሊወጣ እንደሚገባ አሳስበዋል።
በስፍራሽ ደመላሽ
#አሐዱ_የኢትዮጵያውያን_ድምጽ
*ትክክለኛዎቹን የአሐዱ ራዲዮ የማህበራዊ ሚዲያ ገጾች በመቀላቀል ቤተሰብ ይሁኑ!*
ፌስቡክ: https://www.facebook.com/ahaduradio
ድረ ገጽ፡- https://ahaduradio.com/
ዩትዩብ፦ http://shorturl.at/cknFP
ቲክቶክ ፡- www.tiktok.com/@ahadutv.official
ዋትስአፕ፦ whatsapp.com/channel/0029VajDfVZI1rcb05C5B22b
አስተያየት እና ጥቆማ ለመስጠት በ7545 አጭር የፅሁፍ መልክት ይላኩ
